Feb 19, 2013

ክርስቲያኑ ኢትዮጵያዊ መብቱን ለማስከበር ያልቻለባቸውና የማይችልባቸው ምክንያቶች




  • ይህ ጽሑፍ የአቅማቸውን ጥቂት ነገር ለማድረግ የሚተጉትን ላይመለከት ይችላል።
(ደጀ ሰላም የካቲት 8/2005፤ ፌብሩዋሪ 15/2012/ PDF)፦ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገራችን በኢትዮጵያ እየተስፋፋ በመጣው እምነትን በነጻ የማራመድ መብት ገፈፋ ዋነኛ ተጠቂ ከሆኑት ኢትዮጵያውያን መካከል ኦርቶዶክሱ ክፍል ዋነኛ ተጠቃሽ ነው። በወታደራዊው የደርግ ዘመን የነበረውን ግፍና መከራ እንኳን ለጊዜው ብናቆየው “የሕዝብ ብሶት ወለደኝ” ያለው የኢሕአዴግ መንግሥት ከተመሠረተ ወዲህ ቤተ ክርስቲያናችን በዓይነ ቁራኛ ከመታየት እስከ የ“ነፍጠኛ ጎሬ” እስከመባል ድረስ ብዙ ዘለፋ አስተናግዳለች። ከዚያም ገፋ ሲል በአንዳንድ አክራሪዎች ምእመናኗ ታርደዋል፣ አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፣ ከየአካባቢው እንዲፈናቀሉ ተደርገዋል። ለዚህም በስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ የሚያራምደው ፖሊሲ ሁነኛ ምክንያት ነው።

ከዚህ በፊት የተቻኮለ የፓትርያርክ ምርጫ፣ ‘የገበያ ግርግር …’ ይሆናል በሚል ርዕስ ነሐሴ 11/2004 ዓ.ም፤ ኦገስት 17/ 2012/ባቀረብነው ጽሑፍ ላይ እንዳተትነው ኢሕአዴግ ገና በትግል ላይ ከነበረበት ዘመን ጀምሮ ቤተ ክርስቲያናችንን በተመለከተ የያዘው አቋም “ቤተ ክርስቲያኒቱ የጠላት ወገን” እንደሆነች ያስቀመጠ፣ ሌሎች እምነቶችን በተለይም እስልምናን “በተጨቋኝነት” የፈረጀ ስለዚህም ይህንን የተጨቆነ እምነት “በማነቃቃትና ኃይል በመስጠት” ከኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋር እንዲገዳደር ያለመ፣ በመጨረሻም ቤተ ክርስቲያኒቱን ቀስ በቀስ በማዳከም የእርሱ አሽከር እንድትሆን በማድረግ ላይ ያተኮረ ነበር። ይህንን ዓላማውን ለማስፈጸምም ከዋናው የቤተ ክህነቱ አስተዳደር የተለየና የፓርቲውን ዓላማ የሚያራምድ ቤተ ክህነት ለመመስረት በመወሰን የረዥም ጊዜ ዓላማና ግብ ይዞ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። (አዲስ አበባን ከመቆጣጠሩ በፊት በትግራይ ፓርቲውን በፓርቲው የሚመራ ሁለተኛ ቤተ ክህነት አቋቁሞ እንደነበር ይታወሳል)።፡የራሱን አባላትም ወደ ታላላቅ ገዳማት በማስገባት በመነኮሳት ስም ዓላማውን እንዲያስፋፉ ሲያደርግ እንደቆየ የፓርቲው መሥራች ዶ/ር አረጋዊ በርሄ በመጽሐፋቸው አስፋፍተው ገልጸዋል።

ይህ መጽሐፍ ያተታቸው ብዙ ሐሳቦች አሁን በተግባር ላይ መዋላቸው በተግባር እየታየ ያለ እውነታ እንጂ መላምታዊ ሐቲት ወይም በአንድ ወቅት ብቅ ብሎ የጠፋ የፓርቲው ሐሳብ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። በመነኮሳት ስም ያደራጃቸው አባላቱም በቤተ ክህነቱ የተለያዩ እርከኖች ላይ በመቀመጥ ቤተ ክርስቲያናችን የክርስቶስ ሳይሆን የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ዓላማ ማስፈጸሚያ እንድትሆን አስገድደዋታል። ወታደራዊው መንግሥት እንኳን ያላደረገውን የቤተ ክህነቱን መዋቅር ከዋናው እስከ አጥቢያው ካባ በለበሱ ካድሬዎች በማደራጀት ቤተ ክርስቲያኒቱ የክርስቶስ መንግሥት ሳይሆን የኢሕአዴግ መንግሥት አገልጋይ እንድትሆን አድርገዋታል።

ይህም ሳያንስ በልማትና በዕድገት ስም የቤተ ክርስቲያኒቱ ይዞታ ከመደፈሩም ባሻገር የገዳማት ርዕስ የሆነውን የዋልድባን ድንበር በመጋፋት እና የቅድስና ኑሮውን በመግሰስ አበው ገዳማውያን የመከራ ኑሮ እንዲኖሩ በማስገደድ ላይ ይገኛል። ታዲያ እዚህ ላይ ተያይዞ አብሮ የሚነሣው ነገር “ሃይማኖቱን የሚወደው፣ ለእምነቱና ለማተቡ ሟች የሆነው ክርስቲያን ሕዝብ እንዴት ዝም አለ? መንግሥትስ እንዴት የሕዝቡን ስሜት ከቁብ ሳይቆጥረው ቀረ? ሕዝቡንስ እንዴት እንዲህ ሊንቀው ቻለ? ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ‘ድምጻችን ይሰማ’ ሲሉ የክርስቲያኑ ዝምታ ከምን የመነጨ ነው?” ወዘተ የሚለው ጥያቄ ነው።

እንደ እኛ እምነት ከዚህ የበለጠ መከራና ችግር በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ቢወርድም አብዛኛው ክርስቲያኑ ሕዝብ፣ ካህናቱ እና ሲኖዶሱ ምንም ዓይነት የተቃውሞ ድምጽ ሊያሰሙ አይችሉም። የሚቃወሙ ጥቂት ድምጾች ከተገኙም በርግጠኝነት በውጪ አገር ካለው ክርስቲያን፣ ካህን ወይም ጳጳስ ብቻ ሊሆን ይችላል። እነርሱም ምንም ችግር እንደማይገጥማቸው እርግጠኛ ከሆኑ ብቻ ነው። የሩቁን ጊዜ ብንተወውና አሁን በመደረግ ላይ ያሉትን ሁለት የመብት ጥሰቶች ማለትም የዋልድባን ገዳም ማረስ እና ከሕዝቡ ይሁንታ ውጪ 6ኛ ፓትርያርክ ለመሾም (ለማስቀመጥ) የሚደረገውን ሩጫ እንኳን ለመቃወም ክርስቲያኑ ለምን እንዳልቻለ መጠየቅ እንችላለን። (የተቃወሙና የሚቃወሙ ጥቂት ድምጾች ቢኖሩም እነርሱም ከውጪ አገር የሚሰሙ ብቻ መሆናቸውን ሳንዘነጋ ነው ታዲያ)። ስለዚህም የዚህ ዝምታ ምንጩ የተለያየ ቢሆንም ለመወያያ እንዲሆኑ የሚከተሉትን ሐሳቦች እናቀርባለን።


  1. መብት የሚለውን ቁምነገር በትክክል አለመረዳት፤
  2.  

    ክርስቲያኑ ክፍል እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሁሉ “መብት” የሚለውን ቁምነገር በቅጡ ገና አልተረዳም። መብት ጠመንጃ በያዙ ሰዎች ችሮታ የሚታደለው እንደሆነ እንጂ ከእግዚአብሔር ያገኘው ነጻ ሥጦታ መሆኑን አይገነዘብም። ፊደል ያልቆጠረው ማይም ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ኮሌጅ የበጠሰው ምሩቅም ቢሆን ተመሳሳይ ሐሳብ የሚያራምድ ሕዝብ ነው። ስለዚህም መንግሥት የሚያደርስበትን የመብት ገፈፋ ሲችል በመለመን፣ ሳይችል ደግሞ ጀርባውን አጉብጦ በመታገስ ወደመቃብር ይወርዳል እንጂ “መብቴ” ብሎ አይጠይቅም።


    አንድነት የለውም፤

      ከሌላ እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን በተለየ ክርስቲያኑ ክፍል የተጎዳው አንድነት በማጣቱ ነው። ከሊቃነ ጳጳሳት ጀምሮ እስከ ጥቃቅን ማኅበራት ድረስ አንድነት የሚባል ነገር የለም። ጳጳሳቱ ተከፋፍለው ሁለት ሲኖዶስ አቋቁመናል ብለው ከሚነታረኩ ባሻገር ከእነርሱ በታች ያለውም እዚህ ግባ በማይባል በተለያየ ምክንያት የተከፋፈለ ነው። ይህንን ክፍፍል አንድ ሊያደርግ የሚችል ተአምር ካልተፈጠረ በስተቀር ሊያሰጋው የሚችል ተቃውሞ ሊመጣ እንደማይችል ኢሕአዴግም ጠንቅቆ ያውቃል። ስለዚህ ሕዝቡ ብዙ ቢሆንም፣ ምእመኑን ለእምነቱ ሟች ቢሆንም አንድነት እስከሌለው ድረስ ኃይሉ ከንቱ ይሆናል። ሆኗልም። ሙስሊሙ ሕብረተሰብ ከዚህ የተሻለ አንድነት አለው፤ ይህንንም አንድነቱን በዚህ አንድ ዓመት ባሳየው እልህ አስቆጨራሽ የመብት ትግል በገሃድ አሳይቷል። ፕሮቴስታንቱ ክፍል ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የመንግሥት ቀኝ እጅ በመሆን በማገልገል ላይ በመገኘቱ የሥርዓቱ ዋነኛ ተጠቃሚና የሥርዓቱ ዋነኛ ደጋፊ ሆኗል።


      ትክክለኛ መረጃ የለውም፣

        ክርስቲያኑ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ኢትዮጵያዊው ትልቅ የመረጃ እጥረት አለበት። መንግሥት የመገናኛ ብዙኃንን በሙሉ በግል አፍኖ በመያዙ ሕዝቡ የሚያየውም የሚሰማው ነገር የለም። ጋዜጦችና መጽሔቶች አሉ ከሚባሉ ጠፍተዋል የሚለው ይገልጻቸዋል። ያሉትም ቢሆን ውኃ ውኃ የማይል ጽሑፍ ከማንሸራሸር ውጪ መረጃ በመፈንጠቅ ሕዝቡን ከጨለማ ወደ ብርሃን ሊያመጡ የሚችሉ አይደሉም። አገልግሎት እንዲሰጡ የተፈቀደላቸው ሬዲዮኖች “ስፖርት፣ ሙዚቃ፣ ቫለንታይንስ ዴይ አደጋገስ” ወዘተ ካልሆነ ጠለቅ ያለ ሐሳብ ማቅረብ አይችሉም። አይፈረድባቸውም። የተለየ መረጃ ሊገኝበት የሚችለው ነጻ መስኮት (ኢንተርኔቱ) ደግሞ ተቆልፏል። ስለዚህ ይህ መረጃ በማጣት የታወረ ኅብረተሰብ ምኑን ከምኑ ሊያደርገው ይችላል?


        “እግዚአብሔር ያውቃል፣ የእግዚአብሔር ፈቃድ” በሚሉ ርዕሶች ዙሪያ ያለው የተሳሳተ የጽድቅ እና የኃጢአት ትምህርት፣

          አብዛኛው ክርስቲያን  እምነቱን አፍቃሪና አክባሪ ነው። መምህራኑን ይሰማል፣ ቃላቸውንም ይፈጽማል። ነገር ግን ከሚሰጡት ትምህርቶች አብዛኛዎቹ ሆን ተብሎም ይሁን በሌላ ምክንያት ሕዝቡን የሚያደነዝዙ፣ የጥንት ኦርቶዶክስ አባቶቹ እንዳደረጉት ለአገሩ፣ ለእምነቱና ለቤተሰቡ ከመሞት ይልቅ በቅኝ ግዛት እንደተያዙት ሌሎች አፍሪካውያን መጽሐፍ ቅዱሱን ገልጦ ሰማይ ሰማይ ብቻ የሚያይ ደካማ አድርገውታል። አባቶቹ አድዋ ላይ ታቦቱን ይዘው እንዳልውጡ፣ ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ሰዉንም ምድሪቱንም ለፋሺስቶች እንዳይገዙ ገዝተው እንዳልተሰዉ፣ ብዙዎቹ አበው ለአገራቸውና ለእምነታቸው ደማቸውን እንዳላፈሰሱ አይነገረውም። ስለዚህም በስመ ኦርቶዶክስ የሚመራው ክርስትና ከጥንቱ “አትንኩኝ ባይ” ኦርቶዶክስ ጋር ምንም ግንኙነት ያለው አይደለም።

          የተሳሳተ ትርጉም እየተሰጣቸው ሕዝቡ እንዲደነዝዝባቸው ከሚያደርጉት ትምህርቶች መካከል “ሁሉንም ለእግዚአብሔር እንስጠው፣ “እግዚአብሔር ያውቃል፣ እኛ የእርሱን ጊዜ እንጠብቅ” የምትል የራስን ኃላፊነት ሳይወጡ በስንፍና የመቀመጥ አደንዛዥ ትምህርት አንዷ ናት። እግዚአብሔርማ ሁሉን ያውቃል። ምን ጥርጥር አለው። ነገር ግን አዋቂነቱ በዓለም ላይ የሚፈጸመውን ግፍና መከራ ሁሉ እንዲከወን እንደፈቀደ መቁጠር ኑፋቄ ነው።

          በዓለም ላይ በየሰከንዱ ብዙ ወንጀሎች ይፈጸማሉ። ያ ሁሉ ወንጀልና ሰቆቃ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነውን? በርግጠኝነት አይደለም!!! እግዚአብሔር ያውቀዋል ግን? እንዴታ!! እግዚአብሔር የማያውቀው ምን ነገር አለ? የሰው ልጅ ግን በነጻ ፈቃዱ የሚፈጽመው ወንጀል ነው። ለዚህ ጥፋቱ ደግሞ በእግዚአብሔር ፊት ሲቆም ቅጣቱን ያገኝበታል።

          ከዚሁ አያይዘን ስንመለከተው በቤተ ክርስቲያናችን እና በአገራችን ላይ የሚፈጸመውን ግፍ እግዚአብሔር ያውቀዋል። ታዲያ ለምን ዝም አለ ለሚል ግብዝ መልሱ ሰዎች በነጻ ፈቃዳቸው ተጠቅመው ያደረጉት ነገር ነው የሚል ነው። ክፉዎቹ በክፋታቸው ተገፋፍተው ይህንን ሲያደርጉ እኛስ በመልካምነታችን ተጠቅመን የአቅማችንን ለማድረግ ያልቻልነው ለምንድር ነው?

          ከመጽሐፍ አንድ ምሳሌ እናንሣ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አልአዛርን ከሞት ሊያሥነሣው በሄደ ጊዜ የተፈጸመውን ማወቃችን ከላይ ለመግለጽ የፈለግነውን ሐሳብ ግልጽ ያደርገዋል። ታሪኩ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 11 ላይ ይገኛል። አልአዛር ታመመ፣ ሞተ፣ ተቀበረ። ከተቀበረ ከአራት ቀን በኋላ ጌታ ወደዚያ ሥፍራ ሄደ። ከዚያም ከመቃብሩ ላይ ድንጋዩን አንሱ ብሎ ቤተሰቦቹን አዘዘ። ከዚያም አልአዛርን ከመቃብር አልጋ ከሞት ሸለብታ ቀስቅሶ ሕያው አደረገው። ከሞት ማሥነሣቱ ካልቀረ ድንጋዩን እንዲያነሱ ለምን አዘዛቸው? ለምን ሁሉንም ነገር ራሱ አልፈጸመውም? በዚህ የአልአዛር ድኅነት ውስጥ የሰው ድርሻ በቤተሰቦቹ ተሰርቷል፣ የእግዚአብሔር ድርሻ ደግሞ በራሱ በባለቤቱ ተሠርቷል። የሰው ድርሻ መቃብሩን መክፈት፣ የእግዚአብሐር ድርሻ ሙቱን ሕያው ማድረግ ነው። በዘመናችን ግን እያልን ያለነው “ሁሉንም ነገር አንተ ሥራው!!!” ነው። መቃብሩን አንተው ቆፍር፣ ሙቱንም አንተው አስነሳው፤ እኛ ዝም ብለን እንመለከትሃለን።  


          ሥር የሰደደ አድርባይነት መሰልጠኑ፤

            ቤተ ክርስቲያን ለረዥም ዘመን ከቤተ መንግሥቱ ጋር ተቀራርባ የኖረች እንደመሆኗ ሥልጣን ላላቸው ሰዎች ማጎብደድ፣ አድርባይነት እና እታይ-እታይ ባይነት ከጥንቱም ሰልጥኖብናል። በዘመናችን ደግሞ ገዝፎና ተስፋፍቶ ቀጥሏል። የጥንቶቹ መሪዎች ፓርቲ ስላልነበራቸው አባላትም አልነበሯቸውም። የአሁኖቹ መሪዎች ባለ ፓርቲ ስለሆኑ አድርባዮቹ የፓርቲዎቻቸው አባላት በመሆን መስቀልና ሽጉጥ ታጣቂ ካህናት አፍርተናል። በደርጉ ዘመን የኢሰፓ፣ በአሁኑ ደግሞ የኢሕአዴግ አባል ደባትር፣ ካህናትና መነኮሳት አያሌ ናቸው። ይህ አባልነትና አድርባይነት ከተራ ካህናት፣ ደባትርና መነኮሳት አልፎ (በዘመነ ኢሕአዴግ) ከጳጳሳቱ ደርሷል። አባል ያልሆኑትም ቢሆኑ ከዝምታ ውጪ ምንም ምርጫ የላቸውም። ስለዚህ አድርባይነቱ በቅርብ መፍትሔ ስለማያገኝ መከራችንም በቅርብ መፍትሔ ይገኝለታል ብሎ ለማሰብ ይከብዳል።


            መንግሥታት በፈቃደ እግዚአብሔር ሥልጣን ይይዛል የሚለው ትምህርት፣

              ከፍ ብለን ከጠቀስነው ጋር አብሮ የሚሄደው ጉዳይ መንግሥት የሆነ ሁሉ በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው ሥልጣኑን ያዘው የሚል ሐሳብና ትምህርት ነው። ቤተ ክርስቲያንን የሚሰቅላትን “እግዚአብሔር ወዶ ፈቅዶ አስቀመጠው” ማለት ድንቁርና ካልሆነ ምን ይሆናል?


              ኃላፊነትን ለመቀበል መፍራት፣ ኃላፊነትን አለማወቅ፣ ኃላፊነትን ሁሉንም ለእግዚአብሔር መስጠት፣

                እንደተጠቀሰው ከርስቲያኑ ራሱን አቅም እያለው አቅም እንደሌለው፣ ዕውቀት እያለው እንደሌለው ስለቆጠረ ያለበትን ኃላፊነት ለእግዚአብሔር ሰጥቶ “እርሱ ያውቃል” እያለ ተቀምጧል። ኃላፊነቱን አለመወጣቱ ስሕተት መሆኑን የሚገነዘበው ራሱ በጣም ጥቂቱ ነው። ዋልድባ ሲፈርስ፣ አበው አልታረቅ ሲሉ፣ በቆረጣ አዲስ 6ኛ ፓትርያርክ ለማስቀመጥ ሲሯሯጡ “እኔ ምን አቅም አለኝ” ብቻ ነው መልሱ። ይህም ኃላፊነትን ካለማወቅና ኃላፊነትን ለመረከብ ከመስጋት የሚመነጭ ክፉ ደዌ ነው።

                ማጠቃለያ፦

                በአጠቃላይ ስንመለከተው ክርስቲያኑ ክፍል አሁን ያለበት ይህ እና ሌሎች ምክንያቶችም ተጨማምረውበት ለመብቱ ለመቆም፣ ቤተ ክርስቲያኑን ለመታደግና እምነቱን ለማስከበር የሚችልበት ሁኔታ ላይ እንዳልሆነ እንገነዘባለን። በቅርብ ዓመታትም ይሻሻላል ብሎ መጠበቁ ከባድ ነው። በተአምር ካልሆነ በስተቀር አሁን ባለው የክርስቲያኑ አያያዝ ዋልድባንም ያርሱታል፣ አበውንም እንደጀመሩት በማሰር በማንገላታትና በማሰደድ ይገፉበታል፣ የራሳቸው መጠቀሚያ የሆነ 6ኛ ፓትርያርክ በመሾም ሌላ የመከራ ዘመን ያጸናሉ።

                መፍትሔውስ?
                መፍትሔው አጭር ነው። ከአሁኑ መሰባሰብ፣ መደራጀት፣ የችግሮቹን ትክክለኛ ምንጭ መረዳት፤ ለማያውቁት ማሳወቅ፣ ለአጭር ጊዜ ሳይሆን ለረዥም ጊዜ መፍትሔ መሥራት። ‘እዛው ሞላ እዛው ፈላ’ እንደሚባለው ተረት ቶሎ መፍትሔ በመፈለግና ለአጭር ጊዜ ሆይ ሆይ በማለት ችግሩ አይፈታም። የቤተ ክርስቲያን የሆኑትን ከአድርባዮቹ፣ ከአስመሳዮቹና ከጥቅመኞቹ ለይቶ በመረዳት የራስን ኃላፊነት መወጣት። የቀደሙት አበው ከመቃብር ተነሥተው ቢመለከቱን እንዳያፍሩብን እኛም በትውልዳችን የራሳችንን ኃላፊነት መወጣት።

                ይቀጥላል!!!!

                ቸር ወሬ ያሰማን፤ አሜን።

                No comments:

                Post a Comment